በአፋር ክልል 759 ትምህርት ቤቶች በአሸባሪው ሕወሓት መውደማቸው ተገለጸ

ታኅሣሥ 21/2014 (ዋልታ) የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን በአፋር ክልል 4 ዞኖችና 21 ወረዳዎች ባደረሰው ጉዳት 694 ትምህርት ቤቶች በከፊል፣ 65 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ በድምሩ 759 ትምህርት ቤቶች መውደማቸው ተገለጸ።

የወደሙትን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባትና የትምህርት ሥራውን ለማስቀጠል በክልሉ ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላትንና አመራሮችን ያካተተ ቡድን ተዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱ ተገልጿል።

ለመልሶ ግንባታው የሚያስፈልገው አጠቃላይ ወጪ ተሰልቶ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ የአፋር ብሔራዊ ክልል መንግስት ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አሊ መሐመድ ገልጸዋል።

የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ገንብቶ የትምህርት አገልግሎትን በማስቀጠል ረገድ ኅብረተሰቡ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የጭፍራ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መሐመድ አብዱ በበኩላቸው በተለይ አንጋፋ እና በአፈጻጸማቸው ሞዴል በሆኑ ትምህርት ቤቶች የጉዳት መጠኑ የከፋ መሆኑን ጠቅሰው ድርጊቱ ወራሪው ኃይል ለአፋር ሕዝብ ያለውን የጠላትንት ጥግ ያሳየ መሆኑን መግለፃቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።