በአፋር የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አዎንታዊ ለውጥ እያመጣ ነው ተባለ

ግንቦት 8/2014 (ዋልታ) በአገር አቀፍ ደረጃ በትግበራ ላይ የሚገኘው የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በአፋር ድርቅን በመቋቋም ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የክልሉ አርብቶ አደሮች ገለጹ።

ከፑንትላንድ ግዛት የመጡ ልዑካን ቡድን አባላት በቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በኦሮሚያ፣ አፋርና ሱማሌ ክልል የተከናወኑ ተግባራትን ተግባራትን ጎብኝተዋል።

ልዑኩ በአፋር ክልል አሚባራ ወረዳ የእንስሳት መኖ ልማት እንዲሁም በጸሃይ ኃይል የሚሰራ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ሥራዎችን ተመልክተዋል።

የአካባቢው አርብቶ አደሮች በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የሆነው የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በአፋር ድርቅን በመቋቋም ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በአካባቢው ድርቅ እየተከሰተ ከብቶች እየሞቱ ነበር፤ አሁን ግን በፕሮጀክቱ አማካኝነት መኖ እየቀረበ በመሆኑ ከችግር እየወጣን ነው ያሉት።

በሃያ ሄክታር ላይ እየለማ ካለው ቶሎ የሚደርስ የሳር ዘር እስካሁን ለሦስት ዙር ያህል ምርት ተጠቅመናል ብለዋል።

“ዘንድሮ የተከሰተው ድርቅ ከባድ ነበር ይሄ የእንስሳት መኖ ባይደርስልን ኖሮ ከብት የሚባል ነገር አይኖርንም ነበር” ሲሉም አስረድተዋል፡፡

የፕሮጀክት አስተባባሪ ደረሰ ዓሊ እንደተናገሩት፤ የአርብቶ አደርሩን ኑሮ ለማሻሻል በመሰረተ ልማት፣ በውሃ አቅርቦትና የእንስሳት መኖ አቅርቦት እንዲሁም በአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች ላይም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከእንስሳት መኖ ልማት ጋር በተያያዘ በተያዘው ዓመት እስከ 400 መቶ ሄክታር መሬት ላይ በአጭር ጊዜ የሚደርስ ሳር ለማልማት ታቅዶ እስካሁን 300 ሄክታር ላይ ማልማት መቻሉን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በስድስት ክልሎች በ450 ሚሊዮን ብር የሚተገበር ሲሆን ከዚህም 350 ሚሊዮኑ ከዓለም ባንክ፣ 90 ሚሊዮኑ ከዓለም አቀፍ ግብርና ልማት ፈንድ (ኢፋድ) እና 11 ሚሊዮኑ ደግሞ ማኅበረሰቡ በገንዘብና በአይነት የሚደግፈው ነው ተብሏል።