በአፍሪካና አውሮፓ ኅብረት ጉባኤ ኢትዮጵያ ያነሳቻቸው ሐሳቦች ተቀባይነት አግኝተዋል ተባለ

የካቲት 11/2014 (ዋልታ) በ6ኛው በአፍሪካ እና አውሮፓ ኅብረት የጋራ ጉባኤ ኢትዮጵያ ያነሳቻቸው ሐሳቦች ተቀባይነት ማግኘታቸውን በቤልጂየም፣ ሉግዘምበርግና በአውሮፓ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛና አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከጉባኤው ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፍሬያማ የሁለትዮሽ ውይይቶች ማድረጋቸውን አምባሳደር ሂሩት ገልጸዋል፡፡

በጋራ ጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ ያነሳቻቸው የትብብርና የአጋርነት ሁኔታ፣ በሰላምና ጸጥታ ጉዳይ የአፍሪካ ድምጽ ስለሚሰማበት እንዲሁም የወቅቱን የአፍሪካ ኅብረት መሪ ቃል የተመለከቱ ጉዳዮች ተቀባይነት እንዳገኙ ጠቁመዋል።

በጉባኤው የአፍሪካ ድምጽ በሰላምና ጸጥታ፣ ድኅነትን በመዋጋት፣ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በመቀነስ፣ የታዳሽ ኃይል ልማትን በማጠናከር እንዲሁም በስደተኞች ጉዳይ የአኅጉሩንና የኢትዮጵያን መብት ባስጠበቀ መልኩ ተነስቶ የጋራ መግባባት እንደተደረገበት አምባሳደር ሂሩት አስረድተዋል።

በተለይም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል አጋጥሞ የነበረው ጦርነት ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበት መሆኑን ማስገንዘብ እንደተቻለ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።