በአፍሪካ በኮቪድ-19 የሚከሰተው ሞት ከዓለም አቀፍ ምጣኔ መብለጡ ተገለጸ

 

በአፍሪካ በኮቪድ-19 የሚከሰተው ሞት ምጣኔ ወደ 2 ነጥብ 5 በመቶ በማሻቀብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው ምጣኔ መብለጡ ተገለጸ።

የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማእከል ሓላፊ ጆን ንኬንጋሶንግ፣ ወረርሽኙ ሲጀምር በአፍሪካ የነበረው ምጣኔ ከዓለም አቀፉ አማካይ በታች እንደነበር ሐሙስ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

“በአሁኑ ወቅት የሚታየው የሞት መጠን ለሁላችንም እጅግ አሳሳቢ እና አስጨናቂ ሆኗል” ሲሉ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ግብጽ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሱዳንን ጨምሮ ከ3 በመቶ በላይ የሞት ምጣኔ ያላቸው 21 የአፍሪካ አገራት መኖራቸውን ሓላፊው አመልክተዋል።

በአፍሪካ የሞት ምጣኔ ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት ዝቅተኛ ምርመራ እና ወጣት ማኅበረሰብ በመኖሩ መሆኑን ባለሞያዎች ባለፈው ዓመት ሲገልጹ ነበር።

ንኬንጋሶንግ ይህንን ይበሉ እንጂ በአፍሪካ የዓለም ጤና ድርጅት ሓላፊ ማትሺዲሶ ሞኤቲ የአፍሪካ የሞት ምጣኔ ከሌሎች የዓለም አካባቢዎች የከፋ አለመሆኑን በኦንላይን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ሓላፊዋ አሁን የሚታየው የሞት ምጣኔ ጭማሪ የአፍሪካ አገራት በዋናነት እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገራት በገጠማቸው ሁለተኛ ዙር ወረርሽኝ ተግዳሮት ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ከነበረው አኳያ ባለፈው ሳምንት ውስጥ በመላው አፍሪካ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 7 በመቶ ገደማ ሲቀንስ፣ የሟቾች ቁጥር ግን 10 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማእከል አሐዛዊ መረጃ ያሳያል።

አፍሪካ ካላት 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ሕዝብ መካከል 81 ሺህ የኮቪድ-19 ሞት አስመዝግባለች፤ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተመዘገበው ሞት 4 በመቶ ድርሻ ያለው መሆኑን ንኬንጋሶንግ ተናግረዋል።

በአህጉሪቱ 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ሰዎች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸውም በመረጃው ተጠቅሷል።

ባለፈው ሳምንት ብቻ 207 ሺህ አዳዲስ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ሲመዘገቡ፣ ደቡብ አፍሪካ ብቻዋን 100 ሺህ ዜጎቿ በኮሮሮናቫይረስ መያዛቸውን ንኬንጋሶንግ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።