በኡጋንዳ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አባላት ለትምህርት ተቋማት መልሶ ግንባታ ድጋፍ አደረጉ

ሚያዝያ 1/2014 (ዋልታ) በኡጋንዳ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ የድጋፍ አሰባሳቢ ግብረ-ኃይል በሕወሓት የጥፋት ቡድን የወደሙና የፈራረሱ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ በኡጋንዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ያሰባሰበውን አንድ ሚሊዮን ብር ገቢ አድርጓል፡፡
በኡጋንዳ የኢፌዴሪ ልዩ መልክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አለምፀሀይ የግብረ-ኃይሉ አባላት ሕወሓት ጦርነት ከከፈተ ጊዜ ጀምሮ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም በጦርነቱ ተጠቂ ለሆኑት ወገኖች ድጋፍ ማድረጋቸውን በማስታወስ የነገን ትውልድ የሚቀርፁ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የተደረገው ድጋፍ ትልቅ ዋጋ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በኡጋንዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም በኅዳሴ ግድብ ግንባታና በተለያዩ ሀገራዊ ጥሪዎች ላይ እያደረጉት ላለው ንቁ ተሳትፎ ያላቸውን ምስጋና አቅርበው ይህንንም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የግብረ-ኃይሉ ሰብሳቢ አማሃ ይርጋ በበኩላቸው የትምህርት ተቋማት ኢትዮጵያን ወደፊት የሚረከቡ የነገ ትውልድ የሚያፈሩ እንደመሆናቸው ለተቋማቱ መልሶ ግንባታ ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ በመቻላቸው ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡
የውስጥና የውጭ ኃይሎች በቅንጅት በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን ሁለንተናዊ ጦርነት ሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ያለውን ልዩነት አስቀምጦ በአንድ ላይ በመቆም መመከት እንደሚገባውና የችግሩ ተጠቂ የሆኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡