በኢትዮጵያ ላይ ከውስጥና ከውጭ የተከፈተውን ጥቃት በጋራ መመከትና ድል መቀዳጀት እንደሚገባ ተገለጸ

ኡጌቱ አድንግ

ኅዳር 7/2014 (ዋልታ) የአሸባሪው ሕወሓትና የውጭ ኃይሎች በጋራ የከፈቱብንን ጥቃት ለመመከትና ድል ለመቀናጀት በጋራ መቆምና ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል መንግሥት አስታወቀ።

የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኡጌቱ አድንግ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክተው ለኢፕድ እንደገለጹት እንደ አገር የተከፈተብን የኅልውና ጦርነት በድል ለማጠናቀቅ በጋራ መቆምና ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማድረግ ይገባል።

አሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልል የፈጸመው ወረራ ከወዲሁ በጋራ ቆመን ካልመከትነውና ድል ካላደረግነው ወደ ሌሎቹ ክልሎች እንደሚስፋፋ ገልጸው ሁሉም ክልሎች ችግሩ የእኔም ነው በማለት ከውስጥና ከውጭ የተከፈተብን ጥቃት በጋራ መመከትና ድል መቀናጀት ይገባል ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች የፈጸመውን ወረራ በጋምቤላ ክልልም ለማስፋፋት በተላላኪው የጋምቤላ ነፃ አውጭ ግምባር (ጋነግ) በኩልም ጥረት ማድረጉን አውስተው በክልሉ ገላቸውን ለመታጠብ ወንዝ በወረዱ ልጆች ላይ ጥቃት በማድረስ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት ሙከራ ማድረጉን ተናግረዋል።

በቡድኑ የተፈጸመው እኩይ ድርጊት ምክንያት ግጭት እንዳይባባስም በሽማግሌዎችና በመንግሥት በተካሄደው ውይይትም በህብረተሰቡ ጥቆማ 25 የጋነግ አባላት እጃቸውን የሰጡ ሲሆን ቀሪዎቹ እየተፈለጉ መሆኑን ገልፀዋል።