በኢትዮጵያ ታምርት የ2016 ኤክስፖ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ተፈፀመ

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል

ግንቦት 6/2016 (አዲስ ዋልታ) በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የ2016 ኤክስፖ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት እንደተፈፀመ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከግንቦት 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ታምርት የ2016 ኤክስፖ ማጠቃለያ መርኃ ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የአምራች ኢንዱስትሪ ተወካዮች በተገኙበት ተካሂዷል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በኤክስፖው ማጠቃለያ መርኃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ኤክስፖው የተለያዩ ስኬቶች የተመዘገቡበት እንደነበር ገልጸዋል።

በኤክስፓው ከ100 ሺሕ በላይ ግለሰቦችና ተቋማት መሳተፋቸውን ገልጸው ከ57 አገራት የመጡ ድርጅቶች እንዲሁም 157 ዲፕሎማቶች መገኘታቸውን ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ 210 አምራች ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉ ሲሆን 5 ሺሕ 188 አይነት ግብይት የተፈጸመ ሲሆን በገንዘብ ደረጃ ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይግብይት መከናወኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የ2017 ኤክስፖ ከሚያዥያ 30 እስከ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ለሰባት ቀን እንዲካሄድ መወሰኑንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካትና ጥራት ያለው ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የሀገሪቱን ጥቅል ኢኮኖሚያዊ እድገት ድርሻ ለማሳደግ ያለመ ነው።

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ንቅናቄውን በይፋ ካስጀመሩበት ከሚያዥያ/2014 ዓ.ም ጀምሮ ተዘግተው የነበሩ በርካታ አምራች ኢንዱስትዎች ወደ ስራ ገብተዋል።

ንቅናቄው ተኪ ምርቶችን ከማቅረብም ባለፈ ለውጭ ገበያ በማዘጋጀት በአምራች ዘርፉ ላይ መነቃቃት እንዲፈጠር አድርጓል።