በኢትዮጵያ አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ መስፋፋት

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ

መስከረም 12/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ አዲሱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዝርያ (የዴልታ ቫይረስ) በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

ሚኒስትሯ የኮቪድ-19 ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ (የዴልታ ቫይረስ) ሥርጭት እየተስፋፋ በመምጣቱ በዜጎች ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የቫይረሱ ሥርጭት መስፋፋት በቫይረሱ የሚያዙ፣ በፅኑ የሚታመሙና ህይወታቸው የሚያጡ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መሆኑን ነው ሚኒስትሯ የገለፁት።

ለአዲሱ ቫይረስ መስፋፋት ቫይረሱን ለመከላከል የሚተገበሩ “የጥንቃቄ እርምጃዎች መቀዛቀዝ ምክንያት አንዱ ነው” ብለዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው ህዝባዊ ጥንቃቄ የጎደላቸው መሰባሰቦች መብዛታቸውና የህብረተሰቡ በሚፈለገው መጠን ክትባት አለመከተብም ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸውን አመልክተዋል።

በትናንትናው ዕለት 43 ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ ከ800 በላይ ሰዎች ደግሞ በፅኑ መታመማቸውም ነው የገለፁት።

ባለፉት ሶስት ቀናት 108 ዜጎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን እንዳለፈ የተናገሩት ደ/ር ሊያ፣ እስከ አሁን በቫይረሱ የሞቱ ዜጎች ቁጥር ከ5 ሺህ በላይ መሆኑን ገልፀዋል።

የጥንቃቄው አተገባበር መዘናጋት በዚሁ ከቀጠለ ጉዳቱ የከፋ ሊሆን እንደሚችልም አመልክተዋል።