በኢትዮጵያ የተወሰኑ ክልሎች የወባ ወረርሽኝ መጨመሩ ተገለጸ

ግንቦት 30/2014 (ዋልታ) በደቡብ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል የወባ ወረርሽኝ መጨመሩ ተገለጸ፡፡

የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ የተወሰኑ ክልሎች የወባ ወረርሽኝ መጨመሩ ተጠቁሟል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ አሁን ያለውን የአየር ሁኔታ ተከትሎ የወባ ወረርሽኝ መስፋፋቱን ተናግረዋል።

ሙቀትና ዝናብ አንድ ላይ ሲከሰት ያቆረ ውሃ የወባ ወረርሽኝ እንዲራባ ያደርጋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ወቅቱ አርሶ አደሩ ሰብል የሚሰበስብበት እንደመሆኑ መጠን ወረርሽኙ ከጤናው በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንደሚያስከትልም ገልጸዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር ወረርሽኙን ለመከላከል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራ እየሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኅብረተሰቡም ለወባ መራባት መንስኤ የሆነውን የውሃ ማቆርን በማጽዳትና የአልጋ አጎበር በመጠቀም ወረርሽኙን መከላከል አለበት ብለዋል።

በሌላ በኩል በኮቪድ 19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ስለመጣ ኅብረተሰቡ የመከላከያ ዘዴውን መተግበር እና አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል፡፡

የዝንጀሮ ፈንጣጣ በኢትዮጵያ እስካሁን የተያዘ ሰው ባይኖርም ከፍተኛ ስጋት እንዳለ በመጠቆም በሽታው ወደ ሀገር እንዳይገባ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ከገባም መቆጣጠር በሚቻልበት መንገድ ላይ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በመስከረም ቸርነት