በኢትዮ-ሱዳን ድንበር የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

የኢትዮጵያ መንግስት በኢትዮ-ሱዳን ድንበር የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየሰራ እነደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ክልል ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ባለበት በዚህ ወቅት የቀጠናውን አለመረጋጋት የሚፈልጉ አካላት የተሳሳተና አሉታዊ ነገሮችን በአለም አቀፍ መገናኛ እያሰራጩ ነው ተብሏል፡፡

አምባሳደር ዲና የኢትዮጵያ መንግስት በኢትዮ-ሱዳን ድንበር የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየተሰራ እነደሆነም ተናግረዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደመቀ መኮንን ወደ ሱዳን ካርቱም አቅንተው በሰላማዊ መንገድ መፍታት በሚቻልበት መንገድ ላይ ተወያይተዋል ያሉት አምባሳደር ዲና፣ ሱዳን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ህግ በምታስከብርበት ወቅት ሱዳን የዲፕሎማሲ ድጋፏን አሳይታለች፤ ዜጎች ሲሰደዱም አስተናግዳለች፤ ይሄም እንደ በጎ ሊታይ የሚገባው ተግባር ነው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ ውጥረቱ ቢቀንስም ሙሉ በሙሉ እንዲፈታ መንግስት እየሰራ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረው ግጭት የሁለቱን ሀገራት የቀደመ ታሪክ የማይመጥን ነው ተብሏል፡፡

በቀጠናው አለመረጋጋት የሚያተርፉ አካላት ሁኔታዎች እንዲባባሱ እየሰሩ ነው የተባለ ሲሆን ሱዳናውያኑንም መሬቱ የናንተ ነው የሚል ቅስቀሳ በማድረግ በሀገራቱ መካከል ግጭት እንዲፈጠር ስለማድረጋቸው ተነስቷል፡፡

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ከመካከለኛው ምስራቅ 328 ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው መመለስ መቻሉን አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

በሳምንቱ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ የዲፕሎማሲ ስራዎች መሰራታቸው የተነገረ ሲሆን ከተለያዩ ሀገራት ከመጡ በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ማፍሰስ ከሚፈልጉ አካላት ጋር ውይይት መደረጉም ተነግሯል፡፡

ለአንድ ወር ተቆርጦ የነበረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር በመጪው እሁድ እንደሚጀመርም ታውቋል፡፡

(በመስከረም ቸርነት)