በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ ነው

መላኩ አለበል

ሚያዝያ 11/2014 (ዋልታ) “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል ሀገራዊ ንቅናቄ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ እና በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የሀገራዊ ንቅናቄ ዋና ዓላማም የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግሮች መፍታት፣ ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንዲሁም ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩ ዘርፉ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማስቻል ነው ተብሏል፡፡

በንቅናቄው የውጤታማ ሀገራት ተሞክሮ ተቀምሮበት የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነት በማሳደግ ተወዳዳሪ እና ውጤታማ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተናግረዋል፡፡

ለአምራች ኢንዱስትሪው ትኩረት በመስጠት አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በመሳብ፣ ነባሮቹን በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የተሻለ ምጣኔሃብት ለመገንባትም እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከአምራች ኢንዱስትሪው ምርት ለውጪ ገበያ በማቅረብ 390 ሚሊየን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን ይህም የእቅዱን 87 በመቶ መፈፀሙን አመላክተዋል።

በዘርፉ ያሉ ችግሮችን መቅረፍ እና ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሀገሪቷ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ የሚመለከታቸው አካላት በትጋት ሊሠሩ ይገባልም ብለዋል፡፡

የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ ነባር ኢንቨስትመንቶችን መጎብኘታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW