በእስራኤል ለኅዳሴ ግድብ ግንባታ ከ11 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

ሚያዝያ 4/2014 (ዋልታ) ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን 11ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በእስራኤል በአምስት የተለያዩ ከተሞች የድጋፍ ማሰባሰቢያና ግንዛቤ መፍጠሪያ መርሃ ግብሮች በኤምባሲው አስተባባሪነት ተካሂደዋል።

በቴል- አቪቭ፣ እየሩሳሌም፣ ሃይፋና አካባቢው፣ በናታኒያና በቂሪያት ጋት ከተሞች ነው የተካሄደው።

በዚህም በአጠቃላይ ለታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዥና በስጦታ ከ11 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ተችሏል።

በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ረታ ዓለሙ ባስተላለፉት መልዕክት በእስራኤል የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያን የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ ከአንድ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦታ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ወደፊትም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በቢኒ ፊልም ፕሮዳክሽን የተዘጋጀው በዓባይ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን ፊልምና ሌሎች የኪነጥበብ ሥራዎች ለታዳሚዎች መቅረቡን ኤምባሲው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።