በኦሮሚያ ክልል በሰባት ወራት ከ200 በላይ የንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታዎች መከናወናቸው ተገለጸ

ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

መጋቢት 12/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ሰባት ወራት በኦሮሚያ ክልል ከ200 በላይ የንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታዎች መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በተጀመረው የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ ላይ የክልሉን መንግሥት የሰባት ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነው ይህንን የገለጹት።

በሌላ በኩል 101 ኪሎሜትር የመንገድ ግንባታ ለማከናወን ታቅዶ ከ70 ኪሎሜትር በላይ ደረጃውን የጠበቀ አስፓልት መንገድ መገንባቱን፣ ከ3 ሺሕ በላይ የኢንቨስትመንት አማራጮች በክልሉ እንዲፈጠሩ ታቅደው ከ200 በላይ ኢንዱስትሪዎች መቋቋማቸውን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ከ107 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደተቻለም አመልክተዋል።

በክልሉ ከ800 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር እንደተቻለና ለኢንተርፕራይዞች የሚሆን ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መሰጠቱንም አንስተዋል።

በሌላ በኩል በክልሉ በሀርጌ ቦረና እና ጉጂ ዞኖች የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም ፊና የተሰኘ ፕሮጀክት በመቅረፅ አነስተኛ የውሀ ማቆርያዎችን መገንባት፣ ህገወጥ የመሬት ወረራዎችን መከላከል የተሻለ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ መስጠት እና ሌሎች ጉዳዮች በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ክልሉ በሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ፈተናዎች ውስጥ ቢሆንም የተመዘገቡ ስኬቶች አበረታች መሆናቸውን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉን ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻል እና ብልፅግናን ለማረጋገጥ አሁንም በርካታ የቤት ሥራዎች ይጠብቁናል ብለዋል።

በሚልኪያስ አዱኛ