በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖች እና ከተሞች አሸባሪው ሸኔን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው

ነሃሴ 14/2013 (ዋልታ) – በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች እና ከተሞች ነዋሪዎች አሸባሪው ሸኔን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ እያካሄዱ ይገኛሉ።

የአርሲ ዞን እና የአሰላ ከተማ ነዋሪዎች አሸባሪዎቹ ሸኔ እና ሕወሓትን የተቃወሙበትን ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል።

የሁለቱን የሽብር ቡድኖች ጥምረት ያወገዙት ነዋሪዎቹ ከሀገር መከላከያ ጎን በመቆም ሀገራቸውን ከጥፋት ለመታደግ ቃል ገብተዋል።

የምዕራብ ሸዋ እና የአምቦ ከተማ ነዋሪዎችም በአምቦ ከተማ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ የሸኔ እና ሕወሓት የሽብር ተግባርን ተቃውመዋል።

ነዋሪዎቹ ሁለቱ የጥፋት ቡድኖች የፈጠሩትን ጥምረት እንደሚያወግዙ በተለያዩ መፈክሮች ገልጸዋል።

የሆለታ ከተማ እና አካባቢዋ ነዋሪዎችም አሸባሪዎቹ ሸኔ እና ሕወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የፈጠሩትን ጥምረት በሰላማዊ ሰልፍ አውግዘዋል።

የገላን ከተማ ነዋሪዎችም ዛሬ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ አሸባሪው ሸኔ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ እየፈፀመ ያለውን የጠላትነት ድርጊት በፅኑ አውግዘዋል።

ሰልፈኞቹ፣ “የሕወሓት ተላላኪው ሸኔ የኦሮሞ ሕዝብ ጠላት ነው፤ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ነን” የሚሉ እና ሌሎች መፈክሮችንም አሰምተዋል።

የዱከም ከተማ ነዋሪዎችም በተመሳሳይ ሸኔ እና ሕወሓት የፈጠሩት ሀገር የማፈራረስ ተግባርን በሰላማዊ ሰልፍ አውግዘዋል።

ሁለቱ የሽብር ቡድኖች የፈጠሩት የጥፋት ጥምረት በፍፁም እንደማይሳካላቸውም በተለያዩ መፈክሮች ገልጸዋል።

በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች እና ከተሞች በተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ የተሳተፉ ሰልፈኞች፣ “ሸኔ እና ሕወሓት የኦሮሞ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶች ናቸው፣ በመሥዋዕትነት ያገኘነውን ድል በመሥዋዕትነት እናስቀጥላለን፣ የሀገራችንን ኅልውና እያስጠበቀ ካለው ጀግናው የሀገር መከላከያችን ጎን ነን” የሚሉ እና መሰል መፈክሮችን አሰምተዋል በማለት ኢቢሲ ዘግቧል።