በኦሮሚያ ክልል ባለፉት 10 ዓመታት የወባ በሽታ ወረርሽኝ በ83 በመቶ መቀነሱ ተገለጸ

ግንቦት 25/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል ባለፉት 10 ዓመታት የወባ በሽታ ወረርሽኝ በ83 በመቶ መቀነሱን የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መንግስቱ በቀለ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በኦሮሚያ ወባን ከመቆጣጠርና ከመከላከል ባለፈ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት በክልሉ በሚገኙ 249 ወረዳዎች በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
ኃላፊው እንዳሉት የበሽታው ወረርሽኝ አሁንም በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች እየታየ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመመካከር ለወባ ትንኝ መራባት አመቺ ሁኔታ እንዳይፈጠር መስራት አለበት።
አሁንም በበሽታው ተይኌ በጤና ጣቢያዎች እየታከሙ ያሉ ሰዎች እንዳሉ ዶ/ር መንግስቱ የገለፁ ሲሆን ነገር ግን በኦሮሚያ በሚገኙ የደም ባንኮች የደም እጥረት በማጋጠሙ ኅብረተሰቡ ደም በመለገስ የተለመደ ድጋፉን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ኅብረተሰቡ የወባ በሽታ ምልክት የታየባቸው ሰዎችን በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት መውሰድ እንዳለበትም አሳስበዋል።
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ እየተስፋፋ ያለው የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም ለማከም በክልሉ አራት ኮሚቴዎች ተቋቁመው ወደ ሥራ ገብተዋል ብለዋል።
በክልሉ የሚገኙ ሆስፒታሎችና የጤና ባለሙያዎች በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ዶ/ር መንግስቱ ተናግረዋል።
በሀገር ደረጃ በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎች ቢኖሩም እስካሁን ግን የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የተገኘበት አንድም ሰው የለም ሲሉም ገልጸዋል።