በከሃዲው ብ/ጄ ከበደ ፍቃዱ የሚመራው የጠላት ጦር በወልድያ መግቢያ ጥቁር ውሃ አካባቢ ተደመሰሰ – የሀገር መከላከያ ሰራዊት

ነሃሴ 08/2013 (ዋልታ) – በከሃዲው የቀድሞው የ31ኛ ክ/ጦር አዛዥ ብ/ጄ ከበደ ፍቃዱ የሚመራው የጠላት ጦር በወልድያ መግቢያ ጥቁር ውሃ አካባቢ መደምሰሱን የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ገልጿል።

የመከላከያ ሰራዊቱ መረጃ እንደሚያመለክተው በዚህ ውጊያ ከ70 በላይ የጠላት ሃይል ሊደመሰስ ችሏል ፡፡

ጀግኖቹ  የ21ኛ ክ/ጦር የሰራዊት አባላት የድል ችቦዋቸውን ከፍ አድረገው እያውለበለቡ በጥቁር ውሃ ላይ ሌላ አዲስ ታሪክ መስራታቸውን ቀጥለዋልም ብሏል።

ክፍለ ጦሩ በጥቁር ውሃ አካባቢ በወገን ጦር ላይ ጥቃት ለማድረስ በእንቅስቃሴ ላይ የነበረውንና በከሃዲው ጀ/ል ከበደ ፍቃዱ የሚመራውን የጠላት ጦር በአስደናቂ ወታደራዊ ስልት መደምሰስ መቻሉን የ211ኛ ብርጌድ ዋና አዛዥ እና ም/አዛዥ አስታውቀዋል።

አዛዦቹ እንዳስታወቁት ፣ በሰራዊቱ እልህና ቁጭት አስደናቂ የጀግንነት ተግባር ፈፅመናል ብለዋል።

ክ/ጦሩ በጥቁር ውሃ አካባቢ ላይ በፈፀመው የጀግንነት ውሎው ከ70 በላይ የጠላት ሃይል ሲደመሰስ ፣ 19 ክላሽን ኮቭ መሣሪያ ፣ 5  ስናይፐር እና በርካታ ቁጥር ያላቸው ከከባድ እስከ ቀላል የጦር መሳሪያዎች ተማርከዋል ።

ሠራዊቱ አሁንም የህልውና ዘመቻውን በአስተማማኝ የጀግንነት መንፈስ ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል ብሏል።