በክልሉ በሽብር ቡድኑ በወረራ ከተያዙ 5 ወረዳዎች በስተቀር በሁሉም ትምህርት ቤቶች ትምህርት መጀመሩ ተገለጸ  

መስከረም 9/2015 (ዋልታ) በአማራ ክልል በሽብር ቡድኑ በወረራ ከተያዙ 5 ወረዳዎች በስተቀር በሁሉም ትምህርት ቤቶች ትምህርት መጀመሩ ተገለጸ።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክተር ካሴ አባተ እንደገለጹት በትምህርት ዘመኑ ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ከ10 ሺሕ በሚበልጡ ትምህርት ቤቶች ለማስተማር ታቅዷል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት እስካሁን ባለው መረጃ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ተመዝግበው ዛሬ ትምህርት ጀምረዋል።

አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈጸመባቸው አምስት ወረዳዎች ከሚገኙ ትምሀርት ቤቶች በስተቀር በቀሪዎቹ የመማር ማስተማር ስራው ተጀምሯል ብለዋል።

የዘንድሮ የመማር ማስተማር ሥራ የተጀመረው ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሰረት እንደሆነም አስረድተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎችም በየትምህርት ቤታቸው ተሟልተው የመማር ማስተማር ስራው መጀመሩንም አስታውቀዋል።