በክልሉ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ወጣቶች ይሳተፋሉ ተባለ

ሰኔ 20/2014 (ዋልታ) በደቡብ ክልል በዘንድሮው የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ወጣቶች እንደሚሳተፉ የክልሉ ወጣቶች ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡

የደቡብ ክልል ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሱልጣን አሊ በመርኃ ግብሩ 5 ሚሊየን 592 ሺሕ 186 የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

በዚህም ከመንግሥት ይወጣ የነበረውን ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ማዳን እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ወጣቶቹ በቁሳቁስ ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን እና እውቀታቸውን በማቀናጀት የመንግሥትን ወጪ መታደግ እንዲችሉ እንደሚሰራም አብራርተዋል።

በዘንድሮው የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በ13 የትኩረት መስኮች ላይ ልዩ ልዩ ሥራዎችን ለማከናወን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን ከክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

በተለይም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳ፣ የአረጋዊያን ቤት ግንባታና ጥገና እንዲሁም በሌሎችም መስኮች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ይከናወናሉ ተብሏል።