በክልሉ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

መስከረም 13/2015 (ዋልታ) በጋምቤላ ክልል የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች “አጥፊውን ከሰላማዊ ዜጎች መለየት ያስፈልጋል፤ እኛ የትግራይ ህዝቦች በኢትዮጵያ የማንደራደር፤ ሰላም ወዳደድ ህዝቦች ስለሆንን ከሌሎች ህዝቦች ጋር በጋራ ቡድኑን እንታገላለን” ብለዋል።

የከተማዋን ብሎም የሀገሪቷን ሰላም ለማረጋገጥም ከመንግስት ጎን በመሆን የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ጠቁመው መንግስት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ አሸባሪው ህወሓት ሊቀበለው እንደሚገባ አመላክተዋል።

በጋምቤላ ክልል የትግራይ ተወላጆች እስካሁን የከፋ ችግር እንዳልደረሰባቸው ይሁን እንጂ የጅምላ ፍረጃ በመኖሩ በቀጣይ ሊስተካከል እንደሚገባ አስታውቀዋል።

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ላክዴር ላክባክ በበኩላቸው የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር ሆኖ ለሀገር እድገት፣ ለሰላምና ለሁለንተናዊ የሀገር ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያደርግ የነበረ ህዝብ ነው ብለዋል።

ወደ ፊትም የራሱን አሻራ እያሳረፈ ኢትዮጵያን በማሻገር ሂደት የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ገልፀው የሽብር ቡድኑን ህወሓትን ሊያወግዙት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አሸባሪው ህወሓት ባለፉት ዓመታት የህዝቦችን አንድነት የመከፋፈል አጀንዳዎችን ሲያሰርፅ እንደነበር በመድረኩ መነሳቱን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ቡድኑ ለበርካታ ዓመታት የትግራይን ህዝብ የጠበቀን የመከላከያ ሰራዊት ማጥቃቱ መላው የኢትዮጵያን ህዝብ እንዳስቆጣም ተገልጿል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW