በኮምቦልቻ ከተማ የአሸባሪ ህወሓት የጥፋት ተልዕኮ ያነገቡ ሰርጎ ገቦች ተያዙ

ከንቲባ መሐመድ አሚን

መስከረም 4/2015 (ዋልታ) የአሸባሪው ህወሓትን እኩይ ዓላማ ለማምከን አስቀድሞ በተካሄደው ክትትልና ቁጥጥር የሽብር ቡድኑን ተልዕኮ ያነገቡ ሰርጎ ገቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ የጸጥታ ምክር ቤት ሰብሳቢና ከንቲባ መሐመድ አሚን እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት ለ3ኛ ጊዜ በከፈተው ጦርነት በግንባር የገጠመውን ሽንፈት ተላላኪዎቹ በሚፈጥሩት ውዥንብር ለማካካስ እየሰራ ነው።

የከተማውን ሰላም አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ እየተከናወነ ባለው ህዝብን ያሳተፈ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ በ15 ቀናት ውስጥ 105 ተጠርጣሪ ሰርጎ ገቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

ሰርጎ ገቦቹ የተለያየ መታወቂያ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር የያዙ የባንክ ደብተሮች እንደተገኘባቸውም ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ የሽብር ቡድኑን ሴራ ቀድሞ በመገንዘብ አካባቢውን ተደራጅቶ በመጠበቅ የከተማውን ሰላም የማረጋገጡን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ያሳሰቡት ከንቲባው ወጣቶች ተደራጅተው ከተማዋን ከመጠበቅ ባለፈ ለሠራዊቱ ትጥቅና ስንቅ እያደረሱ በመሆናቸው ሊመሰገኑ ይገባዋል ብለዋል።

ከንቲባው አክለውም ኅብረተሰቡ የደጀንነት ሚናውን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን ገልጸው በአውደ ግንባር የመከላከል ውጊያ ከጠላት ጋር እየተፋለመ ላለው ሰራዊት እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ከኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አባይነሽ ፍስሃ በሰጡት አስተያየት ነዋሪዎች የአካባቢያቸውን ሰላም ተደራጅተው በመጠበቅ ሰርጎ ገቦችን ለህግ አሳልፈው እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአካባቢያቸውን ማህበረሰብ በማስተባበር፣ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ስንቅ በማዘጋጀትና የሽብር ቡድኑን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመመከት የደጀንነት ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑንም ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

“ሌት ተቀን አካባቢያችንን ነቅተን በመጠበቃችን የሽብር ቡድኑን ተልዕኮ ተቀብለው ለጥፋት ይሯሯጡ የነበሩ ሰርጎ ገቦች በቁጥጥር ስር እንዲውል ማድረግ ችለናል” ያለው ደግሞ ወጣት አረቡ አህመድ ነው።

ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ አባላት የኋላ ደጀንነታቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ግንባር ድረስ በመሄድ የሽብር ቡድኑን እኩይ ዓለማ ለማክሸፍ ዝግጁነቱን አረጋግጧል።