በኮቪድ የሟቾች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨመር

መስከረም 30/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 በዕየለቱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ከመቼውም ጊዜ በላይ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳሰበ።
በሀገሪቱ ያለው የኮቪድ-19 ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ይህም በበሽታው የሚያዙ፣ በፅኑ የሚታመሙና ህይወታቸውን የሚያጡ ወገኖቻችን ቁጥር ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ በከፍተኛ መጠን እየጨምረ ይገኛል ብሏል።
በኢትዮጵያ አንድ በኮቪድ-19 ቫይረስ የተያዘ ግለሰብ ከተመዘገበበት ዕለት መጋቢት 4/2012 ጀምሮ 354‚033 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ፤ 736 ሰዎች አሁን ላይ በፅኑ ህሙማን ክፍል ይገኛሉ። እንዲሁም 5,950 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
አሁንም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ስጋት መሆኑን በመግለጽ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ በሀላፊነት ስሜት ማስክ በማድረግ፣ የእጅን ንጽህና በተደጋጋሚ በመጠበቅ ፣ በማንኛውም ቦታ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ እና የኮቪድ-19 ክትባት በመከተብ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት እና ለመቆጣጠር የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ እናሳስባለን ብሏል፡፡