በዓሉ ምንም የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ሳያጋጥም በሰላም ማለፉ ተገለጸ

መስከረም 2/2015 (ዋልታ) የአዲስ ዓመት በዓል ምንም የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ሳያጋጥሙ በሰላም ማለፉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ በበዓሉ ዕለት የተመዘገበ ምንም አይነት የእሳትና ድንገተኛ አደጋ አለመኖሩን ገልጸው አደጋ አለመከሰቱ በሌላ ጊዜ በመደበኛ እንቅስቃሴ ከሚያጋጥሙ ክስተቶች ያነሰ ስጋት እንደነበረ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የመዲናዋ ነዋሪዎች አደጋ እንዳይፈጠር በኮሚሽኑ ሲተላለፉ የነበሩ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በአግባቡ በመተግበር ላሳዩት ትብብርም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በተያያዘ ዜና ከትናንት በስቲያ በዓሉ ዋዜማ ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ20 በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ወረዳ ስድስት መዝናኛ ክበብ በዝናብ የረጠበ ችቦ ተገቢ ባልሆነ መልኩ ከመጠን በላይ ቤንዚን በመጨመር በተቀጣጠለው እሳት አደጋ መከሰቱን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በደረሰው ጥቆማ የአደጋ ሰራተኞች በስፍራው ደርሰው እሳቱ ተዛምቶ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ ዕለት ስድስት ኪሎ ሐምሌ 19 መናፈሻ አካባቢ በሚገኝ የፍሳሽ ማስወገጃ ጉድጓድ ውስጥ የ60 ዓመት አዛውንት ሕይወታቸው አልፎ መገኘቱን ገልጸው ፖሊስ አስክሬኑን ተረክቦ የአደጋውን መንስኤ በመመርመር ላይ ይገኛል ብለዋል።

ሕብረተሰቡ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ሲያጋጥም በነጻ የስልክ መስመር 939፤ በቀጥታ የስልክ መስመሮች 011 155 53 00 ወይም በ011 156 86 01 ደውሎ ማሳወቅ እንደሚችል ባለሙያው ማሳወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW