በዓመቱ በሰላምና ፀጥታ ላይ በተሰራ የተቀናጀ ስራ የጠላትን ሴራ ማክሸፍ ተችሏል- ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ

ሐምሌ 14/2016 (አዲስ ዋልታ) በተገባደደው የ2016 በጀት ዓመት በሰላምና ፀጥታ ላይ በተሰራ ቅንጅታዊ ስራ የጠላትን ሴራ ማክሸፍ መቻሉን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ  ገለጹ።

ፕሬዝዳንቱ ይህን የገለፁት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ባለው የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የስራ ዘመን ሶስተኛ ዓመት ሰባተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የ2016 የስራ አፈፃፀም ሪፖርትና የ2017 የስራ እቅድ ባቀረቡበት ወቅት ነው።

በሪፖርታቸውም አሸባሪው የሸኔ ቡድንን ጨምሮ ሌሎች ፀረ ሰላም ቡድኖች የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ሰላም ለማወክ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አንስተው የፀጥታ ኃይሉ ከነዋሪዎች ጋር በከወነው ቅንጅታዊ ስራም አላማቸው እንዲከሽፍ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ሰላምና ፀጥታን በማስከበር ሂደት ውስጥም የፀረ ሰላም ቡድን አባላት በሰላማዊ መንገድ ወደ ማህበረሰቡ እንዲገቡ በተረገላቸው ጥሪ በርካቶች የተሀድሶ ስልጠና መውሰዳቸውን አንስተዋል።

በክልሉ በግብርናው ዘርፍም አስደናቂ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው ሀገሪቱ በምግብ ዋስትና ራሷን ከመቻል አልፋ ወደ ውጭ ለመላክም እያደረገች ያለውን ጥረት የሚያሰካ አፈፃፀም መመዝገቡንም አስታውቀዋል።

በክልሉ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት በተደረገ ተከታታይ ተግባርም በተለያዩ ዞኖችና የከተማ አስተዳደሮች በርካታ ስራዎች መካሄዳቸውን ተናግረዋል። በዚህም ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ጠቁመዋል።

መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍም በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ብልሹ አሰራር የተስተዋለባቸውና የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክፍተት የፈጠሩ አካላት ላይም እርምጃ መወሰዱን አንስተዋል።

በጤናው ዘርፍ፣ በትምህርት፣ በማህበራዊ ጉዳዮችና በሌሎችም በዓመቱ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።

በ2017 የስራ ዘመንም የተገኙ መልካም ውጤቶችን በማስቀጠልና ውስንነቶችን በመቅረፍ ስራዎችን በፍጥነት፣ በጥራትና በብዛት ለመከወን እቅድ መያዙን አንስተዋል።

 

ታምራት ደለሊ ከአዳማ