በዘላቂ አመጋገብ እና የስነ-ምግብ ዘርፍ የላቀ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት ዕውቅና እየተሰጠ ነው

ጥቅምት 27/2015 (ዋልታ) በቆሻሻ መልሶ ማልማትና በዘላቂ አመጋገብ እና የስነ ምግብ ዘርፍ ለተገኙ ውጤቶች የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ዕውቅና የመስጠት መርሀ ግብር እየተከናወነ ይገኛል።
በዕውቅና መርሀ ግብሩ ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ፣ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘው ተሻገር፣ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዲሁም ሚኒስትሮች ተገኝተዋል።
በትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራም ምርጥ ተሞክሮ በ8ኛው የMUFPP (Milan Urban Food Policy Pact) ግሎባል ፎረም ‘ዘላቂ አመጋገብ እና ስነ-ምግብ ዘርፍ’ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ አበባ አሸናፊ መሆንዋ የሚታወቅ ነው።
አዲስ አበባ ሽልማቱን ያገኘቸው ጥቅምት 17 በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ የ8ኛው የMUFPP ግሎባል ፎረም መድረክ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ133 ከተሞች ጋር ተወዳድራ በማሸነፏ ነው።
ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ያሸነፈች ብቸኛ የአፍሪካ ሀገር ሲያደርጋት በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ሽልማቱን ተቀብለዋል።
የዕውቅና መርሀ ግብሩ በአለም አቀፍ ደረጃ ለተገኘው ስኬት የላቀ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት ዕውቅና የሚሰጥበት ነው ተብሏል።
በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ከሚገኘው የዕውቅና መርሀ ግብር በተጨማሪ ከተማ አቀፍ የሌማት ቱሩፋት ማስጀመሪያ አውደ ርዕይ ተከፍቷል።
በሰለሞን በየነ