በደቡብ ክልል 60 ሺህ ለሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች እና የጤና ክብካቤ ሰራተኞች እውቅና ተሰጠ

የጤና ባለሙያዎች እና የጤና ክብካቤ ሰራተኞች እውቅና

ሐምሌ 18/2013 (ዋልታ) – በደቡብ ክልል ኮሮናቫይረስን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ባደረጉት ጥረት 60 ሺህ የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች እና የጤና ክብካቤ ሰራተኞች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

በሆሳዕና ከተማ ዛሬ የተካሄደው የእውቅናና የምስጋና መርኃግብር በክልሉ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ ሰራተኞች የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማድረግ ተጀምሯል።

በመርኃግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ዓለም አቀፍ የሆነውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የጤና ባለሙያዎች የህይወት መስዋዕትነት ጭምር ሲከፍሉ እንደነበር ተናግረዋል። በዚህም በሽታው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከል ተችሏል ብለዋል።

ወረርሽኙን በመታገል ለህዝቡ አገልግሎት የሰጡ የመንግስትም ሆነ የግል የጤናው ሴክተር ባለሙያዎች ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉም ነው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እውቅና የሰጡት።

ከፍተኛ ጉዳት ሳያደርስ ወረርሽኙን መከላከል ቢቻልም አሁንም ከችግሩ ለመውጣት የባለሙያዎችን የጥንቃቄ ምክር መተግበር እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።