በደብረ ብርሃን ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ26 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

ኅዳር 9/ 2014 (ዋልታ) በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከጉምሩክ ኮሚሽን የተገኘውንና አጠቃላይ ግምቱ ከ26 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ የአልባሳትና የምግብ ቁሳቁስ በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ ተደርጓል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)  አሸባሪው ሕወሓት በዜጎች ላይ ዘርፈ ብዙ ቀውሶች እያስከተለ መሆኑን ተናግረው ወቅቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ተረዳድቶ ማለፍ ያለበት ጊዜ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የተደረገው ድጋፍም በተለይ በጉምሩክ ኮሚሽን ማህበራዊ ሃላፊነትን ከመወጣት አኳያ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ በመሆኑ በሚኒስቴሩ ስም አመስግነዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ረ/ፕ/ር) በበኩላቸው ብዙዎች ከቤት ንብረታቸው በመፈናቀላቸው ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ እገዛ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ዋጋ ያልከፈልንባትን ኢትዮጵያ መጠበቅ የለብንም ስለዚህ ሃገራችን እኛን በምትፈልገን ጊዜ ሁሉ ከጎኗ ልንቆም ያስፈልጋል፤ ለልጆቻችንም ነጻና አንድነቷ የጠነከረች ኢትዮጵያ ማስረከብ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቀበታ በበኩላቸው በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውና የተፈናቀሉ ወገኖችን በአንድም በሌላም መንገድ ለማገዝ ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ሲሳይ ወ/አማኑኤል ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት ህዝባችን ያለበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በመረዳት ለተደረገላቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ ማመስገናቸውን  ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡