በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን የተገነባ የደወሌ ድንበር ተሻጋሪ የጭነት ተሸከርካሪዎች ማቆያ ነገ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የትራንስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።
የሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ይግዛው ዳኘው ለኢዜአ እንደገለጹት 90 በመቶ ገቢና ወጪ የንግድ እንቅስቃሴዎች በሚከናወንበት ኮሪደር ተርሚናሉ መገንባቱ ለማህበራዊና የምጣኔ ሃብት የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
ኢትዮጵያንና ጅቡቲ በሚያስተሳስረው በዚሁ ኮሪደር ላይ ለድንበር ተሻጋሪ የከባድ ጭነት ተሸከርካሪ ማቆያ አለመገንባት የጊዜ ጉልበት እና የሃብት ብክነት አስከትሏል ብለዋል፡፡
አሽከርካሪዎች ባልተመቻቸ ሁኔታ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው በተለይ ከኮሮና ክስተት ጋር ተያይዞም በውጪና ገቢ ጭነት ማጓጓዣ ስራ ላይ ስጋት ፈጥሮ መቆየቱን አወስተዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ሚኒስቴሩና የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ከሶማሌ ክልል ጋር በመቀናጀት ነገ ለምረቃ የሚበቃው ተርሚናል የመጀመሪያውን ዙር ግንባታ ከ71 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ መከናወኑን አስታውቀዋል፡፡
ግንባታው የተሽከርካሪ ማቆያን ጨምሮ ለቢሮ አገልግሎት ፣ መታጠቢያ፣ መዝናኛ፣ ህክምና፣ የምግብ እና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚያገለግሉ ስፍራዎች በውስጡ ማካተቱን አስረድተዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ተርሚናሉ ከጅቡቲ በቅርብ ርቀት ላይ መገንባቱ ድንበር የሚሻገሩ ተሸከርካሪዎች እንግልትንና ወጪን ያስቀራል ፡፡
የኮሮና ምርመራን በቀላሉ ማድረግ እንደሚችሉ ገልጸው የተርሚናሉ ስራ መጀመር ለአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡