በዲፕሎማሲው ዘርፍ በሳምንቱ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስራዎች መከናወናቸው ተገለጸ

አምባሳደር መለስ ዓለም

የካቲት 30/2015 (ዋልታ) በዲፕሎማሲው ዘርፍ በሳምንቱ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስራዎች መከናወናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ የኳታር፣ ፓኪስታን እና ቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የሰላም ሁኔታ በመጠቀም መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እንዲሁም የሁለትዮሽ ንግድና የልማት ፋይናንስ ድጋፍ እንዲጨምሩ የተቀናጀ የማግባባት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡

በሳምንቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ ለሀገር ውስጥ ምርት መዳረሻ ለማግኘት እና የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ የዲፕሎማሲ ስራዎች ሲከወኑ ነበር ያሉት አምባሳደር መለስ ይህም የመልሶ ግንባታውን ስራ የበለጠ ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከ5ኛው የተባበሩት መንግስታት የአዳጊ ሀገራት ጉባኤ ጎን ለጎን ውጤታማ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ከነበርንበት የግጭት ዐውድ ወጥተን ወደ ኢኮኖሚ ግንባታ ተሸጋግረናልም ነው ያሉት።

የቻይና፣ ኳታር፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ እና ሌሎች አገራት ባለሀብቶች መዋዕል ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን የገለጹት ቃል አቀባዩ በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኳታር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስክ ላይ በሚሰማሩበት ሁኔታ መክረዋል ብለዋል።

የኳታር ከፍተኛ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በማምረቻው እና በኮንስትራክሽን ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

በቃልኪዳን ሀሰን