በድሬዳዋ ለሕዳሴ ግድብ ባለፉት ስድስት ወራት 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ተሰበሰበ

ሕዳሴ ግድብ

የካቲት 18/2015 (ዋልታ) በ2015 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ገቢ ከቦንድ ሽያጭ ማሰባሰቡን የግድቡ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ሀብታሙ አሰፋ በከተማ አስተዳደሩ በተከናወኑ የገቢ ማሰባሰቢያ ስራዎች በስድስት ወራት ውስጥ ከቦንድ ሽያጭ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸው በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ገቢውን 25 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማድረስ ታቅዷል ብለዋል።

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ቦንድ በመግዛት እና በአጭር ጽሑፍ መልዕክት የገቢ ማሰባሰቢያ ሥርዓቶች ህብረተሰቡ እየተሳተፈ እንደሚገኝና ለግድቡ ግንባታ በአጠቃላይ ያሰባሰበው ገንዘብ ከ92 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በየካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ግቢ የሕዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ የንቅናቄና ቅስቀሳ መርኃ ግብር ይካሄዳል ያሉት ኃላፊው በዚህም ግድቡ አሁን ያለበትን ደረጃ ለማህበረሰቡ በማሳወቅ በቦንድ ሽያጭ ማከናወን፣ የህዳሴውን አርማ ለሽያጭ የማቅረብና በአጭር የጽሁፍ መልዕክት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር ይከናወናል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።