በድሬዳዋ  አራት የንጹህ መጠጥ ውሀ ጉድጓዶች ለአገልግሎት በቁ

ሰኔ 8/2013(ዋልታ) – በድሬዳዋ በተጠናቀቀው በጀት አመት በ53 ሚሊዮን ብር ከተቆፈሩ ስምንት  የንፁህ መጠጥ ውሃ ጉድጓዶች አራቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የከተማው ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አስታወቀ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች በበኩላቸው በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች ለቀናት የውሃ እጥረት እየገጠመ መሆኑን ተናግረዋል።

የድሬዳዋ ከተማ የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የለውጥና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሚሊዮን ስብሃት ለኢዜአ እንደገለጹት  በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ የአዲስ ጉድጓዶች ቁፋሮ ተካሂዷል።

“በአስተዳደሩ በጀትና ከውሃ ፈንድ በተመደበ 53 ሚሊዮን ብር ከተቆፈሩ ስምንት  የውሀ ጉድጓዶች አራቱ ተጠናቀው በሙሉ አቅማቸው ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ጉድጓዶቹ በሰኮንድ 213 ሌትር ውሃ በማመንጨት ለህብረተሰቡ አቅርቦቱን በተሻለ ተደራሽ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

በተጨማሪ 18 ኪሎ ሜትር አዲስ የውሃ መስመር ተዘርግቶ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በበጀት አመቱ ለአገልግሎት በበቁት ጉድጓዶች የከተማው የንጹህ መጠጥ ውሀ አጠቃላይ ሽፋን ከነበረበት 60 በመቶ ወደ 64 በመቶ ማደጉን አስታውቀዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ ባለስልጣኑ በጀት ዓመቱ 17 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ አምርቶ ለደንበኞች ለማሰጨራት አቅዶ  93 በመቶ አሳክቷል።

አሁን ላይ የመልካ ጀብዱ ነባር የመጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በ164 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

ለሚቀጥሉት 30 ዓመታት የነዋሪውን የንጹሁ መጠጥ ውሃ ፍላጎት ለማሟላት እንዲቻል የውሃ መገኛ ስፍራዎችን የሚለይ ጥናት ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

የከተማው ነዋሪዎች በበኩላቸው በባለስልጣኑ የውሀ ተቋማት ቢገነቡም በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች የውሃ ስርጭት ለሳምንት የሚጠፋበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።

የሰባተኛ አካባቢ ነዋሪ ወይዘሮ ዘሐራ ሁሴን የባንቧ ውህ ለአራት ቀን ያክል እየተቋረጠ እንደሚመጣ በመግለጽ ስርጭቱ ሊስተካከል እንደሚገባ አመልከተዋል ።

“በባለስልጣኑ የሚቆፈሩ ጉድጓዶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለህዝቡ ችግር ፈጣን ምላሽ መስጠት ይገባል”  ያሉት ደግሞ የሣቢያን ነዋሪ አቶ መንግስቱ ግዛቸው ናቸው፡፡

የድሬዳዋ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የለውጥና የህዝብ ግንኙነት ባሙያ አቶ ሚሊዮን ስብሃት የነዋሪዎቹ ቅሬታ ትክክል መሆኑን ተናግረዋል።

የውሃ መስመሮች በጨዋማ ንጥረ ነገሮች መዘጋታቸው ለችግሩ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በጨዋማ ንጥረ ነገር ለተደፈኑ መስመሮች በሣምንት ጊዜ ውስጥ መፍትሄ እንደሚሰጥ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተጨማሪም በሌሎች አካባቢዎች ከተዘረጉ የውሃ ማስተላለፊያ መስመሮች ውሃን በመጥለፍ ችግሩ ወዳለበት አካባቢ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።