በጀርመን ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከ20ሺሕ ዩሮ በላይ ተሰበሰበ

ሰኔ 12/2014 (ዋልታ) በጀርመን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሦስተኛው ውሃ ሙሌት መዳረሻ አስመልክቶ በተዘጋጃ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር ከ20ሺህ ዩሮ በላይ ተሰበሰበ፡፡
“ለሕዳሴ ግድባችን የቁርጠኝነት ሕዳሴ” በሚል ሀሳብ የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሦስተኛው ውሃ ሙሌት መዳረሻ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር በጀርመን በርሊን ተካሂዷል።
በጀርመን ፣ በቼክ ሪፐብሊክ፣ በፖላንድ ሪፐብሊክ ፣ በእስሎቫኪ ሪፐብሊክ እና በዩክሬን የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ሚሲዮኑ በሚሸፍናቸው አገራትና ከተሞች ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሦስተኛው ውሃ ሙሌት መዳረሻን በማስመልከት ቦንድ በመግዛት እና በስጦታ ተሳትፎ አድርገው ከ20 ሺሕ ዩሮ በላይ መሰብሰቡን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሁሉም ዘርፍ አገራቸውን ስለሚደግፉና የኤምባሲውን ጥሪ ተቀብለው ለግድቡ ዛሬም አለን በማለት ለሰጡት አገራዊ ምላሽ አመስግነው ዝግጅቱ የኢትዮጵያውያን የአብሮነት ማሳያም ነው ብለዋል።
አምባሳደር ሙሉ በመድረኩ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ በወቅታዊ የሀገራዊ ጉዳይና በሚሲዮኑ የአገልግሎት አሰጣጥ በማስመልከት ማብራሪያና ገለጻ ያደረጉ ሲሆን የተጀመረውን ሀገራዊ አንድነት በተጠናከረ መልኩ በማስቀጠል አገራቸውን መደገፍ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል::