ሐምሌ 27/2013 (ዋልታ) – በደቡብን ሱዳን ጁባ በተካሄደ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እና ለአገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ከ80 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ተሰብስቧል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ምክንያት በማድረግ በደቡብ ሱዳን፣ጁባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተባባሪነት “የህዳሴው ግድባችን የህልውናችንና የሉዓላዊነታችን መገለጫ ነው!” በሚል መሪ ቃል የድጋፍ መግለጫና የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተካሂዷል።
በፕሮግራሙ በጁባና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን የተሳተፉ ሲሆን፤ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ በቦንድ ግዥ 64ሺህ 100 ዶላር እና 25ሺህ የደቡብ ሱዳን ፓውንድ ግዢና ቃል መገባቱ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የሚሆን 15ሺህ 100 ዶላር እና 10ሺህ የደቡብ ሱዳን ፓውንድ በሥጦታ ተበርክቷል።፡
በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር በደቡብ ሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ የሀገር ፍቅር ያላቸው ከመሆኑ የተነሳ የሚደረጉ አገራዊና የልማት ጥሪዎችን በመቀበል እየሰጡ ድጋፍ አድንቀዋል።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳንና በአጠቃላይ በመላው ዓለም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንደ አምባሳደሮች የሚሰሩላት ዜጎች ያሏት አገር እንደሆነች አንስተዋል፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያ ደህንነትና ልማት በጋራ መቆማቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የህዳሴው ግድብ ግንባታና የሀገር ህልውና የማስከበር ዘመቻው እስኪጠናቀቅ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም አምባሳደሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።