በጁባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ ለመከላከያ ሰራዊት ከ32 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረገ

የካቲት 6/2014 (ዋልታ) በደቡብ ሱዳን ጁባ የሚገኘው የኢትዮጵያ 15ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ በአገር ውስጥ በጀግንነት እየተፋለመ ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት የ32 ሺሕ 410 ዶላር ድጋፍ አደረገ።

በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል መህዲ ሰላም አስከባሪ ሻለቃው የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት የሚያኮራ ተልዕኮ እየፈፀመ የሕዝብን ሰላም ከማስጠበቅ ባሻገር በአገር ቤት እየተፋለመ ለሚገኘው ጀግናው ሠራዊት የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ለአገሩ ያለውን ያልተቆጠበ ፍቅር የሚያሰይ ነው ብለዋል።

በያምቢዩ እና ታምቡራ የደቡብ ሱዳን ግዛቶች ሰላም አስከባሪ ሻለቃው አመርቂ የግዳጅ አፈጻጸም በማስመዝገብ የአካባቢውን ኅብረተሰብ ሰላም በአስተማማኝ ማስጠበቅ ችሏል ያሉት ደግሞ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ወታደራዊ አታሼ ብርጋዴል ጄኔራል ዳዊት ወልደሰንበት ናቸው።

የ15ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ከፍያለው ረጋሳ በበኩላቸው ‹‹ግዳጃችንን በአኩሪ ሁኔታ ከመፈፀም ባሻገር በአገር ውስጥ ከሽብርተኛ ኃይሎች ጋር እየተፋለመ ለሚገኘው ሠራዊታችን ድጋፍ ማድረግ በመቻላችን ደስተኞች ነን›› ማለታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።