በጉባኤው የአፍሪካዊያንን አንድነት ይበልጥ በሚያስተሳስር መልኩ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ተደርጓል

ጥር 18/2014 (ዋልታ) በ35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የአፍሪካዊያንን አንድነት ይበልጥ በሚያስተሳስርና የኢትዮጵያን ገጽታ በሚገነባ መልኩ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት መደረጉን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በአፍሪካ ኅብረት መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ በኅብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ እንደሚካሄድ ይታወቃል፡፡

ይሁንና ባለፉት ሁለት ዓመታት የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በአካል ማካሄድ ሳይቻል ቀርቷል፡፡

የኅብረቱ አባል አገራት ከሁለት ዓመታት በኋላ ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ የወሰኑ ሲሆን አዲስ አበባም ዝግጅቷን አጠናቃ እንግዶቿን ለመቀበል እየጠበቀች ትገኛለች፡፡

ለጉባኤው ስኬት ደግሞ የጸጥታ አካላት፣ ሆቴሎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ እንዲሁም የመዝናኛና ቱሪዝም ሥፍራዎች ተግባራዊ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ዝግጅቱን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት ለአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የኢትዮጵያን ገጽታ በሚገነባ መልኩ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ቀደም ብሎ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንግዶች በኢትዮጵያ የሚኖራቸውን ቆይታ ስኬታማ ለማድረግ ዝግጅት ማድረጉንም አንስተዋል፡፡

ሁቴሎች ከአስጎብኚ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት እንግዶቻቸው በመዲናዋ ያሉ ታሪካዊ ስፍራዎችን በመጎብኘት ኢትዮጵያን እንዲያውቁ የሚያደርጉ ፓኬጆችን ማዘጋጀታቸውንም አብራርተዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆቴሎችም የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ገጽታ በሚያስተዋውቅ መልኩ እንግዶቻቸውን ለማስተናገድ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

የዲሊዮፖል ኢንተርናሽናል ሆቴል የመስተንግዶ ሥራ አስኪያጅ ቃልኪዳን አገርነው የኅብረቱን የመሪዎች ጉባኤ ለመሳተፍ ለሚመጡ እንግዶች 40 በመቶ የዋጋ ቅናሽ አድርገናል ብለዋል፡፡

አፍሪካዊያንን አንድነት ሊያጎለብቱ እና የኢትዮጵያን ገጽታ ሊያስተዋውቁ የሚችሉ ዝግጅቶች በማሰናዳት እንግዶቹን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን ነው ያሉት፡፡

የኢንተርኮንትነንታል ኢንተርናሽናል ሆቴል የሰው ሃብት ክፍል ኃላፊ ምህረት ነጋሽ በተመሳሳይ ለጉባኤው ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶችን አፍሪካዊ አንድነትን በሚያንጸባርቁ ዝግጅቶች ለማስተናገድ  በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡