በጋምቤላ ክልል በጎርፍ አደጋ ከ74 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ

ነሐሴ 19/2014 (ዋልታ) በጋምቤላ ክልል በጎርፍ አደጋ ከ74 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር አገልግሎት አስታወቀ።

በክልሉ 8 ወረዳዎች የደረሰውን የጎርፍ አደጋ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጆር ወረዳ ኡንጎጊ ከተማ በመገኘት ተመልክተዋል።

ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

በክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳደር ተንኳይ ጆክ የተመራ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በኢታንግ እና በላሬ ወረዳዎች ተዘዋውሮ የደረሰውን ጉዳት መመልከቱንም የክልሉ መንግሥት ፕሬስ ሴክሬታሪያት መረጃ አመላክቷል።

በክልሉ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በርካታ ነዋሪዎችን ከቤት ንብረታቸው እንዳፈናቀለ እና በሰብል እና በንብረት ላይም ከባድ ጉዳት መድረሱን መመልከታቸውን ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ተናግረዋል።

በጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡