በጋምቤላ ክልል ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል

ሎው ኡቡፕ (ዶ/ር)

መጋቢት 19/2014 (ዋልታ) በጋምቤላ ክልል ባለፉት ሰባት ወራት ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 142 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሎው ኡቡፕ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ባለሃብቶቹ በግብርና፣ ማዕድን፣ ኢንዱስትሪና ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ለመሰማራት የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ ፈቃድ ከወሰዱት መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ባለሃብቶች በግብርና ኢንቨስትመንት እንደሚሰማሩ ጠቁመዋል፡፡

በሰባት ወራት ከ70 በላይ ለሚሆኑ ባለሃብቶች 10 ሺሕ ሄክታር መሬት መተላለፉንና ቀደም ሲል ሲካሄድ በቆየው የኢንቨስትመንት ሂደትና ስምሪት ያጋጥሙ የነበሩ በርካታ ስህተቶች እንዳይደገሙ በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።

“በተለይም ክልሉ የመሬት አጠቃቀም ፕላን በማዘጋጀቱና ለኢንቨስትመንት ሊውል የሚችለውን መሬት በመለየት በአካባቢው በዘርፉ ለመሰማራት የሚመጡ ባለሃብቶች ያለ ምንም መጉላላት እንዲስተናገዱ እየተደረገ ነው” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ፈቃድ የሚሰጠው የራሳቸውን ካፒታልና መዋዕለ ንዋይ ተጠቅመው ሊያለሙ ለሚችሉ ባለሃብቶች መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሁሉም ዘርፎች ፈቃድ የወሰዱት ባለሃብቶች ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ17 ሺሕ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል እንደሚፈጠር ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው በጋምቤላ ወረዳ በልማት ከተሰማሩ ባለሃብቶች መካከል  ተስፋዬ አሻግሪ በሰጡት አስተያየት “የክልሉ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ለኢንቨስትመንት ዘርፍ መጠናከር ቁርጠኛ አቋም አሳይቷል” ብለዋል።

“ከጥቃቅን ችግሮች በስተቀር ለነባሩም ሆነ ለአዲሱ ባለሃብት የሚደረገው መስተንግዶና አቀባበል ካለፉት ዓመታት በእጅጉ የተሻለ ነው” ሲሉም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ቀደመ ሲል ባሉት ዓመታት ባለሃብቱን ተቀብሎ ለማስተናገድ ክፍተቶች የነበሩ ቢሆንም አሁን እየተሰጠ ያለው ድጋፍና ትብብር የሚያበረታታ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በወረዳው በእርሻ ልማት የተሰማሩት ባለሃብት አታላይ አስገዶም ናቸው።