በጋምቤላ ክልል የሚንቀሳቀሱ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መሰረቱ

ሚያዝያ 06/2013 (ዋልታ) – በጋምቤላ ክልል የሚንቀሳቀሱ ስድስት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊና ሌሎች ጉዳዮች ተቀራርበው ለመስራት የሚያስችላቸውን የጋራ ምክር ቤት መስርተዋል።

ፓርቲዎቹ የጋራ ምክር ቤቱን የመሰረቱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ባመቻቸው መድረክ በቀረቡት የጋራ የመግባቢያ ሰነዶች ዙሪያ በመወያየት ከተፈራረሙ በኋላ ነው።

በክልል ደረጃ የጋራ ምክር ቤት ከመሰረቱት መካከል ጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋህነን) ፣ ብልጽግና ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ዴሞክራሲዊ ንቅናቄ (ጋህነዴን) ይገኙበታል።

የጋራ ምክር ቤቱ ከሁሉም ፓርቲዎች በእኩል የተወከሉ 30 አባላት ያሉት ሲሆን፣ ለቀጣይ ስድስት ወራት የጋራ ምክር ቤቱን የሚመሩ ዋና እና ምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም ዋና ጸሐፊ በመምረጥ ሰይመዋል፡፡

ከምክር ቤቱ መስራቾች መካከል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ምክር ቤቱ በክልሉ ብሎም በሀገራዊ የጋራ ጉዳዮችና ሌሎች ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ምቹ አጋጠሚን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በተለይም የፈረሙት የመግባቢያ ሰነዶችን በማክበርና በማስከበር ረገድ ሁሉም ፓርቲ በአግባቡ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ የሚኖሩ የጋራ አጀንዳዎችና የሚያጋጥሙ ችግሮች በጋራ ለመፍታት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው የገለጹት ደግሞ የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ፒተር አማን ናቸው።

‘‘ለክልልችንም ሆነ ለሀገራችን ያለናት እኛው ስለሆነን እንደ ፓለቲካ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን እንደ ዜጋ በያገባኛል ስሜት የህግ የበላይነትን እያከበርን በጋራ ልንሰራ ይገባል’’ ብለዋል።

ስድስትኛው ጠቅላላ ምርጫም ሰላማዊና ዴሞክራሲ ሆኖ እንዲጠናቀቅም የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በጋራ መስራት እንደሚገባም አቶ ፒተር አመልክተዋል።

የኢዜማ ጋምቤላ ቅርንጫፍ ምክትል መሪ ኮማንደር ጋድቤል ቦል የጋራ የምክር ቤቱ የመግባቢያ ሰነዶች ሊከሰቱ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ስጋቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ባመቻቸው የፓርቲዎች የጋራ መድረክ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአሠራር ደንብ፣ የቃል ኪዳን ሰነድ ለማስፈጸም የመጣውን የስነ ስርዓት ደንብ ጨምሮ አራት የመግባቢያ ሰነዶች በአመራሮቹ ተፈራርመዋል።