በጋምቤላ ክልል የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ከሰኔ 28 እስከ ሰኔ 30 ይሰጣል

ሰኔ 22/2013 (ዋልታ) – በጋምቤላ ክልል የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ከሰኔ 28 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚሰጥ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልል አቀፍ ፈተናው ላይ ከ17 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀመጡም ቢሮው አመልክቷል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሴ ጋጄት ክልል አቀፍ ፈተናውን ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸው፣ በ186 የፈተና ጣቢያዎች 523 ፈታኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

በፈተናው ላይ 10ሺህ 319 ወንድ እና 7ሺህ 639 ሴት ተማሪዎች በድምሩ 17ሺህ 958 የቀንና የማታ ተማሪዎች እንደሚቀመጡም አስታውቀዋል፡፡

ፈተናው በሚሰጥበት ቀንም ሆነ የፈተናው የጥያቄ ወረቀት የማጓጓዝ ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን በየዘርፉ የሚገኙ የፀጥታ አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

ፈተናው በሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች ከ150 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል እቅድ መያዙን ጠቁመው፣ ለስኬታማነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻውን ሊያበረክት እንደሚገባም አቶ ሙሴ ማሳሰባቸውን ከጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡