በጋምቤላ ክልል 26 በርሜል ነዳጅና ቤንዚን በቁጥጥር ስር ዋለ

የካቲት 29/2014 (ዋልታ) 26 በርሜል ነዳጅና ቤንዚን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የጋምቤላ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በቢሮው የንግድ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ኡኬሎ ኡቦንግ ተጠርጣሪው ግለሰብ በጋምቤላ ከተማ ከሚገኘው ታፍ ማደያ በሕገወጥ መንገድ በመቅዳት ወደ አኮቦ ለመውሰድ ሲንቀሳቀስ በሕግ ቁጥጥር ስር መዋሉን ገልፀዋል።

ግለሰቡ ንግድ ፍቃድ እንደሌለውና ለመንግሥት ግብር እንደማይከፍል ጠቅሰው በአገሪቱ በወጣው ሕግና ደንብ መሰረት ተገቢው እርምጃ እንደሚወሰድበት ተናግረዋል።

አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ለክልሉ በቂ ነው ተብሎ የሚሰጠውን የነዳጅ ኮታ በሕገወጥ መንገድ በማዘዋወር ኅብረተሰቡን ለእንግልት እየዳረጉ ነው ብለዋል።

በደንብና መመርያ መሰረት ለማስኬድ በሦስቱም ኮሪደሮች ባለሙያ በማስቀመጥ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

ሕገወጥ አሰራሮችን ለማስቆም በከተማው ውስጥ ለሚገኙ ማደያዎች በመመርያው መሰረት እንዲሰሩ ደብዳቤ የመበተን ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።

በክልሉ ውስጥ ማደያ በሌሉባቸው አካባቢዎች በሕግ እና ደንብ መሰረት ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው ጠቅሰዋል።

በከተማው ውስጥ መንግሥትና ሕዝብን ለማጋጨት አላቂ ዕቃዎችን በየመጋዘኑ በመደበቅ ኅብረተሰቡ ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ቀደም ሲል መሸጫ ሱቆቻቸው እደታሸጉባቸው ተናግረዋል።

ከዚህ ሕገወጥ ድርጊታቸው በማይታረሙት ላይ አሁንም አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ገበያውን የማረጋጋት ሥራ እንደሚሰራ መናገራቸውን ከጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።