በጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ የሟች ቁጥር 231 መድረሱን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ


ሐምሌ 20/2016 (አዲስ ዋልታ) በጎፋ ዞን ገዜ ወረዳ ኬንቾ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የሟች ቁጥር 231 መድረሱን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

18 የሚሆኑ ሰዎች አስከሬናቸው እስካሁን አለመገኘቱንና ከ500 በላይ የሚሆኑ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸው ተገልጿል።

የደረሰውን አደጋ ምክንያት በማድረግ የ3 ቀን ብሔራዊ የሃዘን ቀን በማወጅ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ተደርጓል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ አደረጋው በተከሰተበት ቦታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ልዑካቸው ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች አፅናንተው በአካባቢው ባህል መሰረት በመቃብሮች ላይ ችግኝ የመትከል መርሀ ግብር አካሒደዋል ብለዋል።

የተከሰተውን አደጋ ምክንያት በማድረግ የተባበሩት መንግስታት ጨምሮ በርካታ ሃገራት ሀዘናቸውን እየገለፁ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ የተባበሩት አረብ ኢሚሬት ለተጎጂ ወገኖች የሚሆን 85 ቶን ምግብ ነክ እቃ ልከዋል ብለዋል።

በተጨማሪም ክልሎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ባለ ሀብቶችና ግለሰቦች እያደረጉት ባለው እገዛ ምግብነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ እቃዎችን ጨምሮ ከ60 ሚሊየን ብር የሚገመት ዕርዳታ መሰብሰቡን ገልፀዋል።

ዘለቄታዊ መፍትሔ ለማምጣት በርካታ ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ሰላማዊት ካሳ ተናግረዋል።

በዙፋን አምባቸው