በጣሊያን ሚላኖ ከተማ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ያላቸውን ድጋፍ ገለጹ

ሚያዚያ 20 /2013 (ዋልታ) – አንዳንድ የሚዲያዎች ፣ መንግሰታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ከተካሄደው የህግ ማስከበር እርምጃ ጋር ተያይዞ በተዛቡ መረጃዎች በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለውን ጫና የሚቃወም ሰልፍ በጣሊያን ሚላኖ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አካሄዱ::
ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አንዳንድ የሚዲያ ተቋማትእና መንግሰታት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተለይም በትግራይ ክልል ከተካሄደው የህግ ማስከበር እርምጃ ጋር ተያይዞ በተዛቡ መረጃዎች መነሻነት በኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ ላይ እያደረጉት ያለውን አላስፈላጊ ዘመቻ ተቃውመዋል::
እንዲሁም በታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር በተመለከተ ሱዳንና ግብፅ የሚያደርጉትን ጫና እና ሱዳን ዓለም አቀፍ ህግ በመጣስ የፈጸመችው ወረራ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸው፤በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።
አያይዘውም ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፤ ስልጣን የሚያዘው በምርጫ ብቻ መሆኑ አውቀው ማንኛውም አካል ከግጭት እንዲቆጠብ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል የህዋሃት ቅሪቶች አሁንም ከአንዳንድ የውጭ የጥፋት ሽሪኮቻቸው ጋር በመሆን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ጫና ለመፍጠር እየጣሩ መሆኑን ገልጸው፤ ከህግ ማስከበር እርምጃ ጋር ተያይዞ ለተፈጠረው ችግር የሰብአዊ ዕርደታ ድጋፍ በማድረግ ፣ አገራዊ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ እንዲሁም የአገሪን አንድነት በማስጠበቅ ሁሉም በያለበት ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጎን እንደሚቆሙ የሰልፉ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል ፡፡
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የኢትዮጵያ ወዳጆች ተገኝተው እየደረሰ ያለው ጫና መቆም እንዳለበትና ለዚህም ከኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን የጋራ ጥረት እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ሚኒስቴር አስታውቋል።