በጤና ተቋማት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መረጃ ስርዓት ወደ ኤሌክትሮኒክስ ለመቀየር እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

መጋቢት 11/2013 (ዋልታ) – በሁሉም ጤና ተቋማት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መረጃ ስርዓት ወደ ኤሌክትሮኒክስ ለመቀየር እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ባለፉት አመታት ሲተገበር የነበረው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መረጃ ውጤት እንደተገኘበት ጠቅሰው፣ የኤሌክትሮኒክስ መረጃ ስርዓት መተግበሩ አሰራሩን ዘመናዊ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡ ይህንንም ለመተግበር ሙያተኞች ማሰልጠን መቻሉንና ከ30‚000 በላይ ታብሌቶችን ለጤና ተቋማት ማከፋፈሉን ተናግረዋል፡፡

በሚቀጥሉት አምስት አመታት ሁሉም ጤና ተቋማት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መረጃ ስርዓት ወደ ኤሌክትሮኒክስ እንዲቀየር ይደረጋልም ብለዋል።

የመረጃ ስርዓቱ ፍትሀዊና ጥራት ያለው ጤና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ድርሻ ስላለው ለተግባራዊነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰራ ጥሪ መቅረቡን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡