በጥቁር ገበያ የተሰማሩ አካላትን ከፍትህ አካላት ጋር በመተባበር ተጠያቂ የሚያደርግ አሠራር መዘርጋቱን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

ይናገር ደሴ (ዶ/ር)

ታኅሣሥ 6/2014 (ዋልታ) በጥቁር ገበያ የተሰማሩ አካላትን ከፍትህ አካላት ጋር በመተባበር ተጠያቂ የሚያደርግት አሠራር መዘርጋቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አመራሮች ጋር በቀጣይ አብረው በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ሰሎሞን ሶካ ኮሚቴው በፋይናንስ ተቆማት ተደራሽነት፣ በውጭ ምንዛሬ እና በጥቁር ገበያ ተግዳሮት፣ በኦዲት ግኝት እንዲሁም የሕዝብ ቅሬታ የሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚከታተል ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ ባንኩ የዋጋ ንረት ከማረጋጋት፣ የብሔራዊ ባንክ ህጎችን የሚጥሱ ባንኮች የቁጥጥር ሥራ፣ በጦርነቱ የወደሙ ባንኮች መልሶ የማቋቋም ሥራ፣ የብድር አገልግሎት በተለይ ግብርና ዘርፍ ላይ ችግሩን ለመቅረፍ ባንኩ በቀጣይ የተያዙ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ቋሚ ኮሚቴው ማብራሪ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረት ያላቸው በተለይ በግብርናው ዘርፍ ላይ ድጋፍ በመስጠት ብድር መበደር እንዲችሉ በቅርቡ የወጣውን አዋጅ ተግባራዊ በማድረግ ችግሩ እንደሚቀረፍ ገልጸዋል።

በሸሪያ ባንክ ህግ የሚመሩ ባንኮች ደግሞ ራሳቸውን ችለው እንዲቋቋሙ እና የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ለማዘመን የሪፎርም ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በጥቁር ገበያ የተሰማሩ አካላትን ከተለያዩ የፍትህ አካላት ጋር በመተባበር ተጠያቂ የሚሆኑበት አሠራር መዘርጋቱንም አስታውቀዋል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ ባንኮች እና ቅርንጫፎች ላይ እንደ አዲስ ጥሬ ገንዘብ ኦዲት በማድረግ አገልግሎት እንዲሰጡ መልእክት ማስተላለፋቸውን የገለጹት የባንኩ ገዥ የብሔራዊ ባንክ ህግ በሚጥሱ ባንኮች አስተማሪ የሆነ ቅጣት እንደተቀጡ አብራርተዋል፡፡

የባንኩ ግዥ አክለውም የያዝነው በጀት ዓመትና ቀጣይ ዓመት የጦርነት ኢኮኖሚ እያስተዳደሩ መሆናቸው የተለየ እንደሚያደርገው ገልጸው ችግሩን ለመፍታት ከቦርዱ ጋር እንደሚሰሩ እና በቀጣይም ከቋሚ ኮሚቴው ጋር በመደጋገፍ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰሩ ማስረዳታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡