በጦርነቱ የተጎዱ አርብቶ አደሮችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በእቅድ ተይዞ ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ

ጥር 16/2014 (ዋልታ) በጦርነቱ የተጎዱ አርብቶ አደሮችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በእቅድ ተይዞ ሊሰራ እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

በአፋር ክልል በጭፍራ ወረዳ ግመሎች፣ ፍየሎች፣ የእንስሳት መድኃኒቶች፣ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖች እና የአርሶ አደር ሰብሎች መውደማቸውንና መዘረፋቸውን ቋሚ ኮሚቴው ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡

አርብቶ አደሩ በድኅነት አረንቋ ውስጥ እንዲማቅቅ የሚያደርገውን የወራሪውን ቡድን ተፅእኖ ለመቀልበስ በተባበረ ክንድ በመስራትና በመተጋገዝ መልሶ የማቋቋም ሥራው በእቅድ ተይዞ ሊሰራ እንደሚገባ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ሀሙዱ ጋአስ አስገንዝበዋል፡፡

ለተጎዱ አርብቶ አደሮች በጉዳቱ ልክ ፈጥኖ ለመድረስ እና ወደ ነበሩበት መመለስ እንዲቻል ትክክለኛ መረጃ በመሰብሰብ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

የአፋር ክልል ርዕሰ መስታዳድር አወል አርባ ክልሉ በጎርፍ፣ በአንበጣ መንጋ እና በጦርነቱ የተጎዳ መሆኑንና ይህን ችግር ለመቀልበስ ግብርኃይል በማቋቋም በጦርነቱ የተጎዱትን አርብቶ አደሮች መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአፋር ክልል የግብርና መምሪያ ኃላፊ ሃጂ አብዱ ሃሰን በበኩላቸው በጦርነቱ 1400 ሄክታር ማሽላና በቆሎ የአርሶ አደሩ ሰብል በአረምና በተባይ የተባላባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የሰጠውን ሀሳብ በቀጣይ እንደ ግብአትት በመውሰድና እቅድ ውስጠ በማስገባት እንደሚሰራ መግለጻቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡