በፈረንሳይ እና ጣሊያን የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

ግንቦት 16/2014 (ዋልታ) በደቡብ ፈረንሳይ አካባቢ እና በጣሊያን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለተፈናቀሉ ወገኖች እና በጦርነት ጉዳት ለደረሰበት የኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል ድጋፍ አደረጉ።

በደቡብ ፈረንሳይ አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲሁም በጦርነት ጉዳት ለደረሰበት ኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ከተማ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ 1ሺሕ ለሚሆኑ ወገኖች በምግብ፣ መድሃኒትና አልባሳት መልክ ተከፋፍሏል።

በደቡብ ፈረንሳይ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት ላደረጉት ድጋፍ በፓሪስ የኢፌዲሪ ኤምባሲ ምስጋናውን አቀርቧል።

በተመሳሳይ በሮም ከተማ ወጣቶችና በሚላኖ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማኅበር በሉምባርዲያ አስተባባሪነት በተዘጋጁ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ያሰባሰቡትን ከ20 ሺሕ ዩሮ በላይ በኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲውል በጣሊያን ለኢትዮጵያ ኤምባሲ አስረክበዋል፡፡

ኤምባሲው ለተደረገው ድጋፍ አመስግኖ ያሰባሰባውን የገንዘብ፣ የህክምና ቁሳቁሶችና አምቡላሶችን ወደ ኢትዮጵያ መላኩን ገልጿል።

ድጋፉም በጤና ሚኒስቴር በኩል ለተጎዱት ወገኖች እንዲከፋፈል መደረጉን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያውያኑ ተመሳሳይ ድጋፎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ኤምባሲው ጥሪ አቅርቧል፡፡