በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የተገነባው ቤተ መጻሕፍት ተመረቀ

ታኅሣሥ 23/2014 (ዋልታ) በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የተገነባው አብርሆት ቤተ መጻሕፍት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመረቀ፡፡

ግንባታው 18 ወር (አንድ ዓመት ተኩል) የፈጀ ሲሆን ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አሞልቶ የተገነባ ነው።

በምርቃቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እውቀት ከድንቁርና ቀንበር የሚያወጣ ብቸኛው መንገድ ነው ብለዋል፡፡

በአገራችን የሚስተዋሉ ችግሮች ሁሉ የድንቁርና ማሳያ ናቸው በማለትም ከጨለማ ለመውጣት እውቀት መሰረት መሆኑን አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ ያልተጻፉ ታሪኮች አሏት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንኑ ታሪክ ተጽፎ በቤተ መጻሕፍት ውስጥ እንዲቀመጥ ይደረጋል ብለዋል።

ታሪካችንን ማወቃችን ደግሞ በዛ ልክ እንድንራመድ ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ቤተ መጻሕፍቱ በምስራቅ አፍሪካ በግዝፈቱና በዘመናዊነቱ ቀዳሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በእውቀት የበለጸገ ትውልድ ለመፍጠር ቤተ መጽሐፍ ቀዳሚ መሆኑን አንስተዋል።

ከንቲባ አዳነች አገራችን ምንም እንኳን በብዙ ችግሮች ውስጥ ብትሆንም የልማት ሥራዎች ላፍታም አልተዘነጉም ብለዋል።

ይልቁንም በቁጭት በርካታ ፕሮጀክቶች እየተጠናቀቁ መሆኑን ተናግረዋል።

አብርሆት ቤተ መጻሕፍት በ49 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን በአንድ ግዜ ከ2 ሺሕ በላይ ሰዎች ያስተናግዳል።