በ3 የቀድሞ የሜቴክ የሥራ ኃላፊዎች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላለፈ

መጋቢት 28/2014 (ዋልታ) ብርጋዴል ጄነራል ጠና ቁሩንዲን ጨምሮ በ3 የቀድሞ የሜቴክ የሥራ ኃላፊዎች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላለፈ።
ተከሳሾች ክስ ተመስረቶባቸው ጥፋተኛ የተባሉት ስልጣንን ያላግባብ በመገልገል፣ የመንግሥት ሥራን በማያመች አኳኋን በመምራት እና የሕዝብ እና የመንግሥትን ጥቅም የጎዳ ተግባር በመፈጸም የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32 (1) (ሀ)፣ 33 እና 407 (1) (ሀ)፣ (2)፣ (3)፣ 411 (1) (ሀ)፣ (ሐ) እና (3) ላይ የተመለከተውን በመተላለፋቸው ነው።
ተከሳሾቹ የቀድሞው የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የኮርፖሬት ሲቪል ምርቶች ኦፕሬሽን ኃላፊ የነበሩት ብ/ጄነራል ጠና ቁሩንዲ߹ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ሌ/ኮሎኔል አሰፋ ዮሃንስ እና የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ፓወር ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ክንደያ ግርማይ እንዲሁም በቻይና ሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቲምስ ኢንተርናሽናል (ሆ.ኮ) ኩባ. ሊሚትድ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩትና (ያልተያዙት) ሚ/ር ዩዋን ሃን ናቸው።
ተከሳሾች በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ውስጥ በኃላፊነት ደረጃዎች ላይ የመንግሥት ሰራተኞች ሆነው ሲሰሩ ለጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ማምረቻ ፋብሪካ የሚያገለግል ግዥ ሲፈፀም በግልፅ ጨረታ መፈጸም እያለበት የግዥ አፈፃፀም መመሪያ ስር የተቀመጠውን ግዴታ ወደ ጎን በመተው ከጨረታ ውጪ በመመሪያው የተመለከቱት ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ግዥውን ያለ ግልፅ ጨረታ በመፈፀምና እንዲሁም ፕሮጀክቱ “ተርን ኪይ” (ስራው ተጠናቆ ከሙከራ በኋላ ርክክብ የሚደረግበት) ሆኖ እያለ በውሉ የተመለከተው የስራ አፈፃፀም የባንክ ዋስትና ባልቀረበበት ሁኔታ ክፍያ በመፈፀም እንዲሁም ከጠቅላላ የውሉ ዋጋ 10% በሪቴንሽን (ዋስትና) መልክ መያዝ የነበረበትን 5,564,000 USD (አምስት ሚሊዮን አምስት መቶ ስድሳ አራት ሺህ የአሜሪካን ዶላር) ገንዘብ ባለመያዝና ስራው ሣይጠናቀቅ ጠቅላላ ክፍያው ሙሉ በሙሉ (100%) እንዲከፈል አድርገው 4ኛ ተከሳሽ ስራውን ሣይጨርስ ፕሮጀክቱ ገና በ 63.14% ደረጃ ላይ እያለ በራሱ ጊዜ አቋርጦ በመውጣቱ ላልተሰራ ሥራ በኢትዮጵያ ብር 422,791,908.47 አላግባብ በመክፈል ጉዳት በማድረስ እንዲሁም መንግሥት ሥራውን ለማጠናቅቅ ዩናይትድ ኢንተርናሽናል ከተባለ ድርጅት ጋር በገባው ውል መሰረት አላግባብ 6,400,000.00 USD ተጨማሪ ወጪ የሚያስወጣው ሆኖ በመገኘቱ ወይም ጉዳት የደረሰበት በመሆኑ በስልጣን አላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል በመፈፀም በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄነራል ዐቃቤ ህግ ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል።
ካልተያዘው 4ኛ ተከሳሽ ውጭ ያሉት ሌሎች 3 ተከሳሾች በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ቸሎት ቀርበው የወንጀል ደርጊቱን አለመፈፀማቸውን የሰጡትን የእምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ህግ ዝርዝር የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ በማስረዳቱ፤ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን መርምሮ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ ነበር።
ተከሳሾቹ ያቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ በዐቃቤ ሕግ በኩል የቀረበባቸውን ክስና ማስረጃዎች ያላስተባበለ መሆኑን የተቸው ችሎቱ በዐቃቤ ህግ የቀረበው ማስረጃ ተከሳሾቹ የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈጸማቸው በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑን መርምሮ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቷል።
በዚህም መሰረት ቅጣት ለመወሰን ተከሳሾችና ዐቃቤ ሕግ የቅጣት አስተያየታቸውን ለሚያዝያ 07/2014 ዓ.ም እንዲያቀርቡ ቀጠሮ በመስጠት የዕለቱ ችሎት መጠናቀቁን ከኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።