በ38ኛው የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን ውድድር አሸናፊዎች ተለዩ

ሰኔ 5/2014 (ዋልታ) አትሌት ማሞ መንግሥቱና አትሌት ዝናሽ ጋረደው በባሕር ዳር ከተማ የተካሄደውን 38ኛው የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን ውድድር አሸነፉ፡፡

በውድድሩ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እና የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ ድረስ ሳህሉን (ዶ/ር) ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በወንዶች የማራቶን ውድድር አትሌት ማሞ መንግሥቱ ከኦሮሚያ ፖሊስ በአንደኝነት አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አትሌቶች የሆኑት ፅዳት አበጀና አሰፋ ተፈራ እንደየቅደም ተከተላቸው ውድድሩን በሁለተኛ እና ሦስተኝነት አጠናቀዋል፡፡

በሴቶች ምድብ ደግሞ አትሌት ዝናሽ ጋረደው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ በአንደኝነት አጠናቃለች።

አያንቱ ገመቹ  ከፌደራል ፖሊስ ሁለተኛ ሆና ስትጨርስ አትሌት ብዙአገር አደራ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሦስተኛ መውጣቷን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በውድድሩ በሁለቱም ፆታዎች አንደኛ ሆነው ላጠናቀቁ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው የ50 ሺሕ ብር የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ሁለተኛ ለወጡት አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው 25 ሺሕ ብር እንዲሁም ሦስተኛ ሆነው ላጠናቀቁት ደግሞ 20 ሺሕ ብር ሽልማት ተሰጧቸዋል።

በውድድሩ እስከ ስምንተኛ ለወጡ አትሌቶች እንደየደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በውድድሩ 135 የወንድና 101 የሴት አትሌቶች የተካፈሉ ሲሆን የአንጋፋ አትሌቶች ውድድርም ተካሂዷል።