በ400 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የትራንስፎርመር ፋብሪካ ተመረቀ

ሐምሌ 10/2014 (ዋልታ) በሰሜን ሽዋ ዞን አንጎላላና ጠራ ወረዳ በ400 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነባ የትራንስፎርመር ማምረቻና መጠገኛ ፋብሪካ ተመርቋል።

ዳግም ኬኔዲ ጠቅላላ የንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ  ቴዎድሮስ ወልደገብርኤል ፋብሪካው በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የትራንስፎርመር እጥረት በመፍታት ለማገዝ ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ ነው ብለዋል።

የትራንስፎርመር ማምረቻና መጠገኛ ፋብሪካ በዓመት ከ700 እስከ 1 ሺሕ ትራንስፎርመሮችን ማምረት የሚችል መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

እንዲሁም የተበላሹትን በመጠገን ደግሞ ከ1 ሺሕ 500 እስከ 2 ሺሕ የመጠገን አቅም እንዳለው ገልፀዋል።

ፋብሪካው በእንጅነሪንግ ዘርፍ ለተመረቁ 80 ለሚሆኑ ቋሚና 100 ለሚሆኑ ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠሩንም ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በከፍተኛ ወጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ትራንስፎርመር በማስቀረት በዓመት ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለማስቀርትም ያግዛል ተብሏል።

ፋብሪካው በውስጡ አራት የማምረቻ፣ የመገጣጠሚያና የመጠገኛ ወርክ ሾፖች እንዳሉት ተጠቁሟል።