በ6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ተገንብቶ አገልግሎት የጀመረው የፍጥነት መንገድ

መስከረም 10/2014 (ዋልታ) የሞጆ- መቂ- ባቱ የፍጥነት ክፍያ መንገድ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

92 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ይህ የፈጣን መንገድ የመጀመርያው ምዕራፍ በዛሬው ለአገልግሎት ይፋ ሆኗል።

የሞጆ -መቂ- ባቱ የፍጥነት መንገድ 32 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን እያንዳንዱ የተሽከርካሪ መጓጓዣ መስመር 3 ነጥብ 65 ሜትር ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባ ስለመሆኑ ተነግሯል።

ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ ላይ ብቻ መሰረት ያደረገውን የወጪ ገቢ የንግድ አማራጭ በማስፋት የሞጆ ሐዋሳን የፍጥነት መንገድ ተጠቅማ የላሙን ወደብ በስፋት ለመጠቀም የሚያግዛትም ይሆናልም ተብሏል።

ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ለምታደርገው የንግድ ትስስርና የሕዝብ ግንኙነት ፋይዳ ላቅ ያለ ነው ተብሏል።

የክፍያ መንገዱ ግንባታ ከኮሪያ ኤግዚም እና ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ብድር እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግሥት የተገነባ መሆኑ ተነስቷል።

የሞጆ-ሐዋሳ የክፍያ መንገድ አንዱ አካል የሆነው ይህ የክፍያ መንገድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመረቀ ሲሆን አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችሉ ቴክኖሎጂ እስኪገጠምለት ድረስ ቆይቶ ዛሬ አገልግሎት ጀምሯል።

በመንግሥት የተገነቡ የፍጥነት መንገዶችን ተረክቦ የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ቀድመው ሥራ በጀመሩት የክፍያ መንገዶች ባለፉት 7 ዓመታት ከ45 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት በመስጠት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡ ተገልጿል።

በዙፋን አምባቸው